Saturday, December 13, 2014

አገር ውስጥ እየኖሩ መሞት፣ በስደት ጉዞ መሞት፣ በስደት እየኖሩ መሞት!

December 13,2014
“መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው!”
ethiopians and their plight

* አገር ውስጥ “ባርነት”፤ ከአገር ተሰድዶ “ባርነት”

ከጥቂት ቀናት በፊት በአገራቸው መኖር ያቃታቸው 70 ኢትዮጵያዊያን ቀይ ባህርን በጀልባ አቋርጠው ወደ የመን ሲያመሩ በደረሰ አደጋ ሁሉም መሞታቸው ተገልጾዋል። ኢህአዴግ እነዚህ በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ማስረጃ እንደሌለውና “እያጣራ” መሆኑን በቃል አቀባዩ በኩል ተናግሯል፡፡
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከአገራቸው እየተሰደዱ ለባህር፣ ለአውሬ፣ … የተዳረጉት ወገኖቻችን ብዛት ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ ይህንን ሁሉ አልፈው ወዳሰቡት የደረሱት ደግሞ በስደት የሚኖሩባቸው በተለይ የአረብ አገራት ይህ ነው የማይባል ሰቆቃ ይደርስባቸዋል፡፡ ይህንን ሁሉ የሚሰማው ወገን አሁንም በየኤምባሲው ቪዛ ለማስመታት በተገኘው ቀዳዳ ከአገሩ ለመውጣት ይጥራል፡፡ በዚህ በኩል ያልተሳካለት ድንበር በማቋረጥ አስጨናቂውንና አስፈሪውን ጉዞ ይጀምራል፡፡
“አገር እየለማች” ነው ለሚለው ኢህአዴግ ይህ ምንም ዓይነት ምላሽ የሚሰጥበት ባይሆንም አሁንም “ለጊዜው የምጠብሰው ትልቅ አሣ አለና ጊዜ የለኝም” በማለት መስማት የተሳነው መሆኑን ይናገራል፡፡ አሽቃባጭ ካድሬዎቹም በየማኅበራዊ ድረገጾችና መገናኛ ብዙሃን “መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው” ይሉናል፡፡
በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የስደት ህይወት ለመምራት እየወሰኑ የሚሄዱት ወገኖቻችን ከሚያስቡበት አገር ሲደርሱ ስለሚሆነው ሰሞኑን የወጣው የ2014 “የባርነት መለኪያ ዘገባ” በዘመናዊ ባርነት ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 390ሺህ እንደሚገመት ተናግሯል፡፡ (የጎረቤት ኬኒያ65ሺህ እንኳን አልደረሰም)
ከአረመኔ የባህር ላይ አስተላላፊዎች ያመለጡት ወይም “በልማት እየተመነደገች” ካለችው አገራቸው ኑሮን ማሸነፍ እያቃታቸው ወደ አረብ አገራት “በቪዛ” የሚወጡት በ“Global Slavery Index” መለኪያ መሠረት ለዘመናዊ ባርነት የሚጋዙ ናቸው፡፡
አገር ውስጥ ያለው “ዘመናዊ ባርያ” ኑሮን ማሸነፍ ያቃተውና የሰው ልጅ ሊሰራው የማይገባውን ሥራ የሚሠራ እንደሆነ ዘገባው ጠቆሟል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚሰደደውና እዚያም በኑሮ ስቃይ ውስጥ የሚገባው ወላጅ ልጆቹን ለጎዳና ተዳዳሪነት፣ ለልመናና ለወሲብ ንግድ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ወደ ት/ቤት መላክ የሚገባቸው ህጻናት ሊሠሩት ቀርቶ ሊያስቡት የማይገባ እጅግ ዘግናኝና ሰቅጣጭ ሥራዎችን እንዲሰሩ ይገደዳሉ፡፡refugees and their boat
በአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘው የመርካቶ አካባቢ የመሸታና የሴተኛ አዳሪ ቤቶች ክምችት እንደሆነ የጠቆመው ዘገባ የዘመናዊ ባርነቱን ሁኔታ ይዘረዝራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከአገር ውስጥ “ዘመናዊ ባርነት” ያመለጡት ወደ አረብ አገራት “ለውጭ አገር ዘመናዊ ባርነት” ገንዘባቸውን እየከፈሉ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ይሰጣሉ፡፡
በዚህ የባርነት ንግድ ያልጠገበው ኢህአዴግ በቅርቡ በሳውዲ የሆነውን የወገን ሰቆቃ ቸል በማለት የተቋተረጠበትን ገቢ እንደገና ለመጀመር “ሕግ እያረቀቀ” መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ባርነቱን በመቀጠል ሽያጩን ለማጧጧፍና ትርፉን ለማጋበስ ረቀቅ ባለ ሁኔታ ዝግጅቱን አድርጓል፡፡ ባለሥልጣናቱም የአረቡን አገራት ጎብኝተው “በባርነት ንግዱ” ላይ ተስማምተው መጥተዋል፡፡ ይህንን “መልካም ዜና” የሰሙት “ተስፈኛ ዘመናዊ ባሪዎችም” ዓይናቸውን ጨፍነው ወደ ጭለማው ለመግባትና ህይወታቸውን ለባርነት አሳልፈው ለመስጠት ሙሉ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ እስከዚያው ለመጠበቅ ያልቻሉትና “ከአገር ውስጥ ዘመናዊ ባርነት” ሞትን የመረጡት አሁንም ድንበር እያቋረጡ ወደ ባህር ይጓዛሉ፡፡
ባለፉት የመጋቢትና የሚያዚያ ወራት ቁጥራቸው ከመቶ የሚያልፍ በተመሳሳይ አደጋ ሰጥመዋል፤ ለቀብር ሳይበቁ በውሃ ተበልተዋል፡፡ ያገራቸው “ህዳሴና ልማት” ሊያኖራቸው ያልቻለው አውሮጳን አልመው እስከዚያው የአረቢያ ምድርን ተስፋ አድርገው በምድርና በባህር የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ ከመሄድ በቀር የመቀነስ ሁኔታ አይታይበትም፡፡ አውሮጳን ሳያልሙ “ለዘመናዊ ባርነት” ወደ አረቢያ የሚሰደዱት ምንም ተስፋ በሌለበት ሁኔታ እንኳን ከእነርሱ በፊት ሄደው የተሳካላቸውን ሰዎች በማሰብ እነርሱም ከእነዚያ መካከል እንደሚሆኑ በመገመት ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ከደረቁ ምድር ገና ለመሳፈር ሲነሱ ለባህር ወንበዴዎች ገንዘባቸውን ይከፍላሉ፤ ከዚያም ሲያልፍ የአካል ክፍላቸውን እያወጡ ይሸጣሉ፤ እዚያው በኢንፌክሽን ይሞታሉ፤ ከዚህ ያመለጡትና “ባርነትን” ተስፋ ያደረጉት ደረቅ ምድር ሳይደርሱ በባህር ይሰጥማሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ የተረፉት ጥቂቶች ከባህርና ከአጓጓዥ አውሬዎች አምልጠው “ለዘመናዊ ባርነት ብቁ” ይሆናሉ፡፡ በባርነት “ያተረፉትን” ገንዘብ ወዳገራቸው ይልካሉ፤ ያገራቸውን “ኢኮኖሚ በድርብ አኻዝ” ያሳድጋሉ፤ “በልማቱ መስክ” ይሳተፋሉ፤ … “መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው!”

No comments: