Wednesday, November 19, 2014

የትብብሩ ፓርቲዎች እነማን ናቸው? እንዴትስ ተሰባሰቡ?

November 19,2014
- ወደ ዘጠኝ ዝቅ ያሉትስ በምን ሁናቴ ነው? 

ዮናታን ተስፋዬ (የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ)

አንዳንዴ ነገሮች በተጨባጭ ሳይሆን በመሰለን ነገር ብቻ እየተመለከትን እውነታውን እንዘነጋውና ችግር ናቸው ለምንላቸው ነገሮች ሌላ መላ ለማምጣት ብዙ እንደክማለን፡፡ መድከማችን ግን የችግሮቹን ወይም የሁነቶቹን አነሳስና አካሄድ ካላገናዘበና ከግምት ካላስገባ ከንቱ ድካም ይሆንና በስህተት ላይ ሌላ ማረሚያ ስህተት እየፈጠርን ችግሩን የባሰ እናወሳስበዋለን፡፡

ይህን ታሳቢ በማድረግ ሰሞኑን በትብብሩ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስም ማብራሪያም ይሆን ዘንድ አጀማመራቸውንና 9 ከመሆናቸው በፊት ስንት እንደነበሩ፣ እነማን በምን ምክንያት ትብብሩን እንዳልተቀላቀሉ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ በዚህ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን የማስተናግድ ሲሆን በተረፈ ግን ሊጠየቁ የሚገቡ አካላት በአግባቡ እንዲጠየቁ እና በማነሳቸው ነጥቦች ላይ አስተያየትና መልስ እንዲሰጡ እጋብዛለሁ፡፡

በ9ኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር የተግባር ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት ሰማያዊ፣ አንድነትና መድረክን ጨምሮ 12 የሚደርሱ ፓርቲዎች ከ3 ወራት በላይ በጠረጴዛ ዙሪያ በልዑኮቻቸው በኩል ተወያይተውበታል፡፡ በነዚህ ወራት ውስጥም በጥቅሉ ባለፉት የፖለቲካ ውጣ ውረዶች የነበሩትን ድክመቶች በመፈተሽ እና በምን መልኩ በጋራ መስራት እንደሚቻል በሰፊው በመነጋገር ሰነዱን ለህዝብ ይፋ አድርገዋል፡፡ (በትብብሩ የተዘጋጁ ሰነዶችን በሰማያዊ ፓርቲ የፌስቡክ ገፅ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡)

ይህን ሰነድ በውይይት አዳብረው ለማጽደቅ የደረሱት ፓርቲዎች ዝርዝር ይህን ይመስላል፡-
1- ሰማያዊ ፓርቲ
2- መድረክ (እንደ ቡድን በመወከል)
3- አንድነት ለፍትህ እና ዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት)
4- መኢአድ (የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት)
5- መኢዴፓ (የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ)
6- ኢብአፓ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ)
7- ኦፌኮ (የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ)
8- አረና ትግራይ
9- የኦሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት
10- መዐህድ (የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት)
11- የከምባታ ህዝቦች ኮንግረስ
12- የጌድኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
ናቸው፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት ፓርቲዎች መካከል በመድረክ የታቀፉት እና አንድነት ፓርቲዎች በጋራ ሲመክሩበት ከነበረው ስብስብ እና ባፀደቁት ሰነድ መሰረት በአንድ ምክንያት ብቻ ወደፊት መቀጠል ተስኗቸው ነበር፡፡

በመድረክና በአንድነት መካከል የተፈጠረው ቅራኔ በንግግር ባሳለፉበት ወራቶች ውስጥ ረግቦ የነበረ ቢሆንም ፓርቲዎቹ ወደ ተግባር ተኮር ፊርማ ሲያቀኑ ግን ዳግም አገርሽቶ ሂደቱንም ጭምር ማጓተት ጀመረ፡፡ መድረክ ‹‹ከጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ውጪ ከአንድነት ጋር መስራት ይቸግረናል፣ በመሀከል ያለው ጉዳያችን ሳይፈታ ወደ ፍርርም መሄድ አንችልም - በመሆኑም አንድነት ከመድረክ መውጣቱን ይፋ ያድርግ›› ሲል፤ አንድነት በበኩሉ ‹‹መድረክ እገዳውን ያንሳ ወይ በይፋ አንድነትን ከመድረክ ያስወጣው እንጂ እኛ ወጥተናል የምንልበት ምንም ምክንያት የለም›› ሲሉ ተከታከሩ፡፡ በዚህ መሃል ፓርቲዎቹ ለምርጫ ቦርድ በፃፉት ደብዳቤ ላይ ከአንድነት በስተቀር ሁሉም ፓርቲዎች ማህተምና ፊርማቸውን በማኖር ወደ ተግባር መንደርደር ጀመሩ፡፡ ነገር ግን በግልፅ ትብብሩን ለህዝብ ይፋ ለማድረግና ቅርፅ ለማስያዝ ለመፈራረም በመድረክና በአንድነት በኩል ያለው ችግር በፓርቲዎቹ መሃከል በሚደረግ ውይይት አለመፈታቱ ሂደቱን አዘገየው፡፡

በትብብር ለመስራት ሲወያዩ የነበሩት ፓርቲዎች (በሙሉ) ከነደፉት የትግል ስትራቴጂ መካከልም ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ አንደኛው ምርጫውን በተመለከተ የአጭር ጊዜ እቅድን ያካተተ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የረዥም ጊዜ ሆኖ የሀገሪቱን መፃዒ እድል ለመወሰን የሚያስችል እቅድን ያካተተ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም ከ3 ወር በላይ የተካሄደው ውይይት ወደ ተግባር ለመግባት የመቋጫ ፊርማ የሚደረግበት ጊዜ ከላይ ባነሳሁት የመድረክና የአንድነት ጉዳይ ከሚጠበቀው በላይ መጓተት ከማስከተሉም በላይ ፓርቲዎቹ በየግል የሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ ድብታን አስከተለ፡፡

በመሆኑም ፓርቲዎቹ በየግላቸው (መድረክ በጠቅላላ ጉባኤው አንድነት በምክር ቤቱ) ችግሩን እንዲፈቱ የተቀሩት ፓርቲዎች ግን ወደ ስራ እንዲገቡ ስምምነት ላይ ስለተደረሰ ከእነዚሁ ፓርቲዎች ውጪ 9ኙ ወደ ፊርማ አመሩ፡፡

ይህ በሆነበት ሰሞንም አንድነት ውስጥ የነበረው የውስጥ ችግር አቶ ግዛቸው ሺፈራው (ኢንጂነር) በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን በመልቀቃቸው በምትኩም አቶ በላይ ፈቃዱ የአንድነት ፕሬዘዳንት ሆነው በመሾማቸው የተነሳ አንድነት በትብብሩ ውስጥ የነበረው ሚና ቀነሰ፡፡ የተፈጠረው የስልጣን ክፍተት ማለትም አቶ ግዛቸው (ኢንጂነር) እንዲሁም ለትብብሩ የተወከሉት ሰዎች ለአዲሱ የፓርቲው መሪ አቶ በላይ በምሉዕነት መረጃ እና ሂደቱን ባለማካፈላቸው (አቶ ግዛቸው/ኢንጂነር/ ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ልብ ይሏል) ከትብብሩ ፊርማ ሳይሳተፉ ሲቀሩ፤ መድረክ በበኩሉ አንድነት ላይ ባሳደረው ጥርጣሬ የተነሳ ጠቅላላ ጉባኤውን ለመጠበቅ በማሰብ ከፊርማው ለጊዜው ታቀበ፡፡ ይህ ከሆነ ከሳምንታት በኋላ አንድነት ይበልጥ ትብብሩን ቢርቅም (ምክንያቱን አንድነት ቢመልሰው መልካም ነው) በመድረክ አባል ፓርቲዎች (በተለይም አረና እና ኦፌኮ) በኩል ደግሞ በትብብር ለመስራት ቁርጠኝነት ነበር፡፡

በሌላ በኩል ከሁለት ሳምንት በፊት የተደረገው የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ በትብብሩ ላይ መልካም ያልሆኑ ነገሮች (ለሚዲያ የማይበቁ እና ገንቢ ያልሆኑ) የተንፀባረቁበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዋናው ጉዳይ ይህ አይደለምና ውሳኔው ምን ነበር የሚለውን ማየቱ መልካም ነው፡፡ ከትብብሩ ጋር ሊያያዝ የሚችል የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ካሳለፋቸው ውሳኔ ውስጥ አንዱ የአንድነት ጉዳይ ሲሆን መድረኩ አንድነት በ15 ቀን ውስጥ ውሳኔውን ካላሳወቀ ከስብስቡ በራሱ እንደወጣ ይቆጠራል የሚል ነበር፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የመድረኩ ፓርቲዎች በጋራ ስለትብብሩ ያሳለፉት ውሳኔ የለም፡፡ ይህንንም የመድረኩ አባል ፓርቲዎች ወይም መድረክ ራሱ ቢመልሰው መልካም ይሆናል፡፡

ለማጠቃለል - ከላይ ከሰፈሩት 12 ፓርቲዎች መሀል 9ኙ ትብብሩን ተፈራርመው ወደ ተግባር ቢገቡም ባጠቃላይ የነበረው ሂደት ግን ይሄን ይመስል ነበር፡፡ ከዚህ ያጎደልኩት ካለ በትብብሩ የረዥም ጊዜ ውይይት ተሳታፊ የነበሩና ክንውኑን ከስሩ በደንብ ሊያስረዱ የሚችሉት አቶ ግርማ በቀለ (የኦሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ሊቀመንበር) የበለጠ እንዲሉበት እጋብዛለሁ፡፡ የጨመርኩት ወይም ያዛባሁት ካለም እታረማለሁ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በመድረክ የታቀፉ ፓርቲዎችም ሆኑ አንድነት ወደ ትብብሩ እንዲመጡና ትግሉን ተቀላቅለው እንዲያጠናክሩት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህ ትብብር ለነፃነት በጋራ መታገልን ያለመና እየተንሰራራ ያለውን የትግል መንፈስ ወቅቱን በመጠነ መልኩ አጠናክሮ ለማስቀጠል ነውና ማንም በምንም ምክንያት ከመሳተፍ እዲገለል ሰማያዊም ሆነ የትብብሩ ፓርቲዎች አይሹም፡፡ በግሌም ቢሆን ትግሉን መቀላቀል ያለውን ፋይዳ ለናንተ መንገር ሳያሻኝ የፓርቲ ፖለቲካውን ትግል ጋብ አድርገን በጋራ ለነፃነት ትግሉ እንድንቆም በትህትና ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ኑ! በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን ነፃ እናውጣ፤ መፃዒ እድላችንንም በጋራ እንወስን!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: