Tuesday, November 25, 2014

ቦታ ጠበብኝ ( ሄኖክ የሺጥላ )

November 25,2014

ታላቁ መንግስታችን የኢትዮጵያዊነት እሴቶች የሆኑት ነገሮች ሁሉ መደርመሱን ቀጥሎበታል። የነጻነት እና የማንነት ተምሳሌት የሆኑት አብይ ኩነቶችን ጭቃ ከመቀባት እስከ አፈር ማልበስ፣ ከማብጠልጠል እና ማናናቅ እስከ መቀበር፣ ከ መዝረፍ እና ማዘረፍ እስከ ፍጽሞ ማጥፋት እየሄደበት ያለውን መነገድ አስፋፍቶ ቀጥሎበት ትናንት ደሞ የ ታላቁን ወ-መዘክር መጻሕፍት ቤት ታሪካዊ መጽሐፍቶች ( የባለ ብዙ ዘመን እድሜ መጽሐፍቶች ) በኪሎ እንደሸጠው ሰምተናል። እነዚህ መጽሐፍቶች በውስጣቸው የያዙት ቁም ነገሮች ትውልድ የሚቀርሱ ፣ የማንነት መቅርጫዎች፣ የአእምሮ መሳያዎች ነበሩ። ዛሬ ግን ስኩዋርና እጣን መጠቅለያ ይሆኑ ዘንድ ተፈርዶባቸው በየ -ስርጡ ተወሽቀው ይገኛሉ። የሚገርመው እነዚህም መጽሐፍቶች ” ቦታ ጠበበኝ ” በሚል ምክንያት በኪሎ እንደተሸጡ ሰምተና ። ትናንት የ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ሲፈርስ እንዲፈርስ የተደረገው በዚሁ ሰበብ ነው፣ ” ቦታ ጠበብኝ “፣ የሚንልክንም ሃውልት ለማንሳት ታስቦ ” አይ እሱን ለተሻለ አላማ ( አማራውንና ኦሮሞውን ) ለማጋጨት ብንጠቀምበት ይሻል ” ተብሎ በይደር እንዳለፈ ሰምተናል። ከዚህ ሌላ ብዙ አሳፍሪ ድርጊቶች በየዕለቱ ይከናወናሉ፣ ኢትዮጵያ ግብረ ሶዶማዊነት ከመስፋፋት አልፎ የራሳቸውን መንደር መስርተው የሚኖሩባት ሀገር ሆናለች ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሴተኛ አዳሪነት መአከል ሀገር ሆናለች ፣ ኢትዮጵያ የብልሹ ትውልድ መኮትኮቻ እና ማሳደጊያ ማሳ ሆናለች ፣ ኢትዮጵያ በዙ ነገር ሆናለች ፣ እኛ ግን ከሆነችሁ ሁሉ የሚቆረቁረን እና የሚያስጨንቀን ያቆምነው ግንብ ሆኖዋል ፣ የ ተከልነው መሰረት ሆኖዋል ፣ ግለኝነት ሆኖዋል ። ነገራችን ሁሉ በ አሸዋ ላይ እንደተሰራ ቤት ከሆነ ቆይቶዋል ። ምንም የማያስጨንቀን ብቻ ሳንሆን ፣ ለገዢው መንግስት ፍቅራችንን ለመግለጽ የተቃዋሚ ሰዎች ገጽ ላይ ስድብ መለደፍ ስራዬ ብለነዋል ።
መልክት ለመንግሥታችሁ
ውድ መንግሥቴ ሆይ ትናንት የ-ወመዘክርን መጽሐፍቶች በኪሎ ስትሸጥ ምናልባት ታሪኩን አጠፋለሁ ብለህ አስበህ ይሆናል ፣ ምናልባት ያንተን ታሪክ ጽፈህ ቤተ መጽሐፍቱን ልትሞላው አስበህ ይሆናል ፣ ምናልባት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ፈጽማ እስክትጠፋ ድረስ ተግተህ እየሰራህ
ይሆናል። ግን ማወቅ ያለብህ አንተ ዛሬ በኪሎ የሸጥከው መጽሐፍም ሆነ ፣ ከልለህ የሸጥከው መሬት ወረቀት ላይ ወይም ምድር ላይ ሳይሆን ያለው ያለው ደሜ ውስጥ ነው ። ታሪኩን ሸምድጀዋለሁ ፣ አቀዋለሁ ፣ ሁሉንም ቃል በቃል አስታውሰዋለሁ ። አንተ በኪሎ የሸጥከው መጽሐፉን እንጂ ተማሪውን አይደለም ፣ ተማሪው በጭንቅላቱ ይዞ የሚዞረውን እውነት ፣ ህዝቡ በደሙ ተሸክሞ የሚኖረውን ማንነት ፣ አሱን አሱን በኪሎ ልትሸጠው አትችልም ። እርግጥ መጽሐፉም ይሁን ሐውልቱን ካሉበት ልታነሳቸው ትችላለህ ፣ ከኔ ልብ ውስጥ ግን በፍጹም አትችልም ፣ አየህ አንተ ትናንት በኪሎ የሸጥከው መጽሐፍ መልክቱን በሚገባ አስተላልፎዋል ፣ አየህ እኔ እስካለሁ ድረስ ፣ እሱ እስካለ ድረስ ፣ እኛ እስካለን ድረስ መጽሐፉ ይኖራል ። ወረቀቱን ልትቀደው ትችላለህ ፣ስኩዋር መዝነህ ልትሸጥበት ትችላለህ ፣ ግን ወረቀቱ ለኛ ያስተላለፈውን እውነትም ሆነ ወረቀቱ ላይ ያለውን እውነት ምንም አይነት ነገር ልታሸክመው አትችልም ። ጴጥሮስ መኖሩን ለማወቅ ከፈለክ እስክንድር እየው ፣ አንዱዋለምን እየው ፣ አስራት ወልደየስን እየው ። ሃብተ ጊዮርግስ ድነግዴ በሕይወት መኖራቸውን ማወቅ ከፈለክ በቀለ ገርባን እየው ፣ አየህ መጽሐፉ የት እንዳለ ? ወመዘክር መደርደሪያ ላይ ሳይሆን እኔ ደም ውስጥ !
ዛሬ የጠበበሕ ቦታ ነው ነግ ግን ምግቢያው መውጫው ይጠብሃል ፣ እስክናሸንፋችሁ ድረስ ዝም አንልም !!!!!

No comments: