Tuesday, October 21, 2014

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩም እንደገና ተከሰሰ

October 21,2014
(ኢ.ኤም.ኤፍ) በኢትዮጵያ ውስጥ በነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለው ወከባ እስር አሁንም እንደቀጠለ ነው። በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ከሃያ በላይ ጋዜጠኞች አገር ለቀው ተሰደዋል። ሌሎች ጋዜጠኞች “አሸባሪ” የሚል ቅጽል ተሰጥቷቸው በእስር ቤት ይማቅቃሉ። በጣት የሚቆጠሩት ብቻ አገር ቤት ሆነው የሚመጣውን ለመቀበል የተዘጋጁ ይመስላል። በቅርቡም ተመስገን ደሳለኝ ወደ እስር ቤት እንዲወርድ መደረጉ የሚታወስ ነው።
አሁን ደግሞ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና ማዕከላዊ ሄዶ ክሱን እንዲወስድ በስልክ ተነግሮታል። ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በራሱ ብዕር ስለሁኔታው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል። “እንግዲህ፣ ‹‹ማዕከላዊ ናና ክስህን ውሰድ›› ተብያለሁ” ብሎ ይጀምራል፤ ዛሬ በላከው ማስታወሻ ላይ።
ኤልያስ ገብሩ
ኤልያስ ገብሩ
*********************************
ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ ሞባይል ስልኬ አቃጨለች፡፡ ከጎኔ ወዳጄ አቤል አለማየሁ ነበር፡፡ የመስመር ስልክ ነው፡፡ አነሳሁት፡፡ ‹‹አቶ ኤልያስ›› የሚል የሴት ድምጽ አደመጥኩ፡፡ ‹‹አዎን›› በማለት መለስኩላት፡፡ ‹‹ቆይ አንዴ መስመር ላይ ጠብቅ›› አለችኝ፡፡
ወዲያው አንድ ወንድ አነሳና ሰላምታ ሰጥቶ አናገረኝ፡፡ የሚደውለው ከፌዴራል ፖሊስ መሆኑን ጠቆመኝና ‹‹ባለፈው ተቋርጦ የነበረው ክስህ ስለተዘጋጀ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቁጥር 76 መጥተህ ውሰድ›› አለኝ፡፡ ስለጉዳዩ ጥቂት ቃላቶች ተለዋወጥን፡፡ 
‹‹እሺ ሰሞኑን መጥቼ እወስዳለሁ›› አልኩት፡፡ ‹‹ዛሬም የምትችል ከሆነ መምጣት ትችላለህ›› አለኝ፡፡ ጎሳዬ ሲልም ስሙን ነገረኝ፡፡
…በውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ መታሰር ሳይኖርብህ ትታሰራለህ፡፡ ዋስትና መከልከል ሳይኖርብህ ትከለከላለህ፡፡ ዳኛ የሰጠው የተጨማሪ የምርመራ ቀን ሳይደርስ ‹‹ስንፈልግህ ትመጣለህ፤ ዋስ አምጥተህ ውጣ›› ትባልና ከእስር ትለቀቃለህ፡፡ ከአምስት ወራት በኋላ ደግሞ ትጠራና ‹‹ከስህ ተዘጋጅቷል ና›› ትባላለህ፡፡ …ነገ የሚሆነውን ነገር ደግሞ አታውቅም፡፡ …እንግዲህ እንዲህ ነች የዛሬዋ ኢትዮጵያ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
==============
ከላይ ያቀረብነው የኤልያስ ገብሩን ጽሁፍ ሲሆን፤ አሁን በስደት የሚገኘው የስራ ባልደረባው ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን ደግሞ እንዲህ ብሏል።
=============
ፍትህ በየት አለሽ?
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ማዕከላዊ መጠራቱንና የጥሪው መንስኤም ከዚህ ቀደም ለእስራት የተዳረገበት ዕንቁ መጽሔት ላይ በሰዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አማካኝነት የወጣ ጽሁፍ እንደሆነ ነግሮናል፡፡
የኤልያስን ክስ፣የፍርድ ቤት ውሎና የማዕከላዊ ቆይታውን በቅርበት ይከታተል እንደነበረ ሰው የአሁኑ ጥሪ ግርም ቢለኝ የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት ወደድኩ፡፡
የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ አንቀጽ 43/ቁጥር 1 ‹‹በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ፣ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ካልወሰነ በስተቀር በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 59/2/እና 3 ድንጋጌዎች መሰረት ፣ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት፡፡..በማለት በማያሻማ መልኩ ቢደነግግም ጽሁፉ በወጣበት ወቅት የዕንቁ ዋና አዘጋጅ የነበረው ኤልያስ በማዕላዊ መርማሪዎች ትዕዛዝ ቀበቶውን ፈትቶ ታሳሪዎችን እንዲቀላቀል ተደረገ፡፡
ኤልያስ ከእስሩ ሁለት ቀናት በኋላ አራዳ ምድብ ችሎት እንዲቀርብ ተደረገ ፣ከሳሽ የማዕከላዊ መርማሪ ተጠርጣሪው የተያዘው በመጽሔቱ ላይ በወጣ ጽሁፍ የተነሳ በጅማ ዩኒቨርስቲ ብጥብጥ ተነስቶ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናገረች፡፡
ኤልያስ በበኩሉ አዋጁን ጠቅሶ ለእስር መዳረግ እንደሌለበትና ጉዳዩን በውጪ ሆኖ መከታተል እንደሚችል ገለጸ፡፡
ዳኛው ለደቂቃዎች ካቀረቀሩበት ቀና ብለው‹‹እውነት ነው አዋጁ ጋዜጠኛው መታሰር እንደሌለበት ይናገራል፣ነገር ግን ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አለብኝ ስላላ የ7 ቀን ጊዜ ሰጥቻለሁ በማለት አረፈው፡፡
ኤልያስ ወደ ማዕከላዊ ተመለሰ፡፡በነጋታው ግን የማዕከላዊ ሰዎች 30.000ብር ዋስ እንዲያቀርብ አድርገውት ለቀቁት፡፡
በቀጠሮው ቀን ኤልያስ ፍርድ ቤት የመሄድ ፍላጎት ነበረው፤ ግን አጠገቡ የነበርን ሰዎች ‹‹እነርሱ ሲፈልጉ ክሱን ሊቀሰቅሱት ይችላሉ እስከዛው ዝም ብለህ ጠብቅ” አልነው፡፡
እውነትም እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ኤልያስን የፈለገውም አልነበረም፡፡አሁን መዝገቡን ከቆለፉበት ክፍል አውጥተውት ‹‹ና››ብለውታል፡፡
አወይ ፍትህ?አቤት ፍርድ ቤት?ከወራት በፊት በዚሁ ጉዳይ ኤልያስን ያናገሩት ዳኛ አሁን ሲመለከቱት ምን ይሉ ይሆን?ምን ችግር አለው ‹‹ባለፈው ቀን ምን ላይ ነበር ያቆምነው››ብለውም ይጀምሩ ሆነዋል፡፡
——-መልካሙን ሁሉ ወዳጄ ሆይ እመኝልሃለሁ፡፡——–

No comments: