Friday, October 17, 2014

በተቃዋሚዎች የሚረጨውን መርዝ ለማርከስ ለዩኒቨርስቲ ምሁራንን ለሌሎች ዜጎች የውይይት መድረኮች መዘጋጀታቸውን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ

October 17,2014
99 በመቶ በላይ የኢህአዴግ አባላት በሞሉበት ፓርላማ ውስጥ ብቸኛ የሆኑት የአንድነት ፓርቲ ተመራጩ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ በቅርቡ መንግስት ለዩኒቨርስቲ  መምህራን፣ ተማሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች የሚሰጠውን የፖለቲካ ስልጠና አስመልክቶ ላቀረቡት ጥያቄ መልስ የሰጡት ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ውይይቱን ማድረግ ያስፈለገው ትምክህተኞች፣ ጸረ ሰላም ሃይሎችና ጠባቦች የሚረጩት መርዝ ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ባለስልጣናትና ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን በመጥላታቸው በብሄሮች መካከል መቃቃር እና ግጭቶች እንዲፈጠሩ እየሰሩ በመሆኑ መንግስት በሁለቱም ላይ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።በጋምቤላ በመዠንገር አካባቢ የተከሰተው ግጭት በመንግስት ባለስልጣናትና በተቃዋሚዎች የተፈጠረ መሆኑን፣ እጃቸው አለበት የተባሉ የመንግስት ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ጠ/ሚ ተናግረዋል።

የጠ/ሚንስትሩ ንግግር ኢህአዴግ በየቀኑ እርሱ በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማጣቱ እንዳሳሰበው፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው አለመረጋጋት እየጨመረ መምጣቱን ለማመን መገደዱን ያሳየነ ነው ሲል በስፍራው የተገኘው ዘጋቢያችን ገልጿል።

አቶ ግርማ ሰይፉ መንግስት በአምስት አመታት ውስጥ ያቀደውን እቅድ ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ በበቂ ሁኔታ ሊሰራ አለመቻሉን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማንሳት ጠይቀዋል።የባቡር መንገድ ከ100 ኪሜትሮች በላይ አለመሰራቱ፣ ይህን ድክመት ለመሸፈንም በአዲስ አበባ ያለውን የባቡር መንግድ ደጋግሞ በማሳየት ድክ መትን ለመሸፈን ሙከራ መደረጉን አቶ ግርማ ገልጸዋል።

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የባቡር ፐሮጀክቶች በብድር የሚሰሩ በመሆኑን በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ብድር ለማግኘት ችግር መኖሩን በመጠቆም ትኩረቱ ከአዲስ አበባ ጅቡቲና ከመቀሌ አዋሽ ባሉት የባቡር ፕሮጀክቶች ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ እነዚህም ፕሮጀክቶች ከጅምር ያለፉ አለመሆኑን ከንግግራቸው ለመረዳት ተችሎአል።

70 በመቶ የስኳር ፋብሪካዎች በዚህ አመት እንደሚጠናቀቁና ስኳር በማምረት ወደ ውጭ መላክ እንደሚጀመር ጠ/ሚ ቢናገሩም፣ በመላ አገሪቱ ስኳር በመጥፋቱ ሻሂ ቤቶች ስኳር በኮታ ለመውሰድ እየተገደዱ፣ ሌሎች ተጠቃሚዎች በቂ ስኳር ለማግኘት በማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል።

ጋዜጠኞች እየታሰሩ፣ የውይይት ምህዳሩ እየጠበበ መምጣቱን የገለጹት አቶ ግርማ፣ መንግስት ከጦር ይልቅ ሃሳብንና ውይይትን እንደሚፈራ ያሳያል ብለዋል። አቶ ሃይለማርያም ጋዜጠኞች ህዝብን ከህዝብ ለማጋሸትና ሽብር ለመፈጸም በመንቀሳቀሳቸው መታሰራቸውን በመግለጽ የአቶ ግርማን አስተያየት ውድቅ አድርገዋል።

ምንጭ  ኢሳት

No comments: