Monday, September 15, 2014

በጎደሬ ወረዳ የዘር ግጭት ተነሳ፤ መከላከያ ገብቷል

Sep14,2014
የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ከነቤተሰቦቻቸው ተገደሉ
goderie

በጋምቤላ ዞን በጎደሬ ወረዳ ነጋዴዎችና ሰፋሪዎች ከአካባቢው ተወላጅ የመዠንገር ጎሳ አባላት ጋር ተጋጩ። በግጭቱ ከ17 ሰባት በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በግጭቱ የመዠንገር ዞን አስተዳዳሪና የጎደሬ ወረዳ ዳኛ ከነቤተሰቦቻቸው የግጭቱ ሰለባ መሆናቸው ታውቋል። ግጭቱን ለማብረድ የመከላከያ ሠራዊት የገባ ሲሆን፣ የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ግጭቱን ለማብረድ በጉዞ ላይ እንዳለ በተሰጠ መመሪያ እንዲመለስ ተደርጓል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለጎልጉል እንደገለጹት በወረዳው በመሬት ባለቤትነትና በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ከመሀል አገር በመጡ ሰፋሪዎችና ነጋዴዎች መካከል አለመግባባት ከተፈጠረ ዓመታትን አስቆጥሯል። የፌዴራል አገዛዙም ሆነ የክልሉ አመራሮች ችግሩ ሳይሰፋ ሰላማዊ መፍትሄ ባለማፈላለጋቸው ችግሩ ሊካረር ችሏል። ኢህአዴግ የሚከተለው በዘር ከፋፍሎ የመግዛት ፖሊሲ ለችግሩ መባባስ በዋንኛነት ተጠቃሽ ነው።
ባለፈው ሃሙስ በአንድ የመሃል አገር ሰፋሪና የአካባቢው ተወላጅ በሆነ አርሶ አደር መካከል ድንገተኛ ጸብ ተነስቶ ነበር። በጸቡ የመዠንግር ጎሳ አባል የሆነው አርሶ አደር ህይወት አለፈ። በጎሳ አባላቸው መገደል የተበሳጩ ዘመዶች ውሎ ሳያድር በወሰዱት የበቀል ርምጃ አንድ ሰፋሪ የመሃል አገር ሰው ህይወት አለፈ። እንደ ዜናው አቀባዮች ከሆነ በዚሁ በመሬት ጉዳይ በተከሰተው የሁለት ግለሰቦች ህልፈት ተከትሎ ችግሩ ተካረረ።
በተመሳሳይ ቀን ማምሻው ላይ ከመሃል አገር የመጡት ሰፋሪዎች የዞኑን አስተዳዳሪ፣ ባለቤታቸውንና ሁለት ልጆቻቸውን መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ በስለት ገደሉ። በተመሳሳይ አንድ የጎደሬ ወረዳ አስተዳዳሪ ከባለቤታቸውና ከልጃቸው ጋር ተገደሉ። በደቦ የተጀመረው የስለት ግድያ እየሰፋ የሟቾችን ቁጥር 17 እንዳደረሰውና በስለት የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ከ40 በላይ መሆኑን በስልክ የገለጹት ያካባቢው ነዋሪዎች “አሁን ፍርሃቻ አለ። ቤት ለቤት የተካሄደው ግድያ የት ጋር ያቆማል? የመከላከያ ሠራዊት ሚናም ግልጽ አይደለም” ብለዋል።
የጋምቤላ ዞን ልዩ ኃይል ግጭቱን ለማብረድ እየገሰገሰ ባለበት ወቅት ከአዲስ አበባ በተሰጠ ትዕዛዝ ወደ ጋምቤላ እንዲመለሱ መደረጉን ያመለከቱት እኚሁ ክፍሎች፣ “የጋምቤላ ልዩ ኃይል ግጭቱ ያለበት ቦታ ሲደርስ በራሱ ክልል ሰዎች ላይ መጤዎች ጉዳት ማድረሳቸውን ሲመለከት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ግጭት ሊፈጠር ይችላል” በሚል ስጋት የልዩ ኃይሉ ወደ ጋምቤላ የተመለሰበትን ምክንያት ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በገጀራና በተለያዩ የስለት መሳሪያዎች የተካሄደው ግድያ የሚዘገንን እንደነበር፣ ቀን ጠብቆ ተጎጂው አካል ከመበቀል ወደኋላ እንደማይል፣ በስለታማ ቁሶች የሚከናወነው ግድያ ሊሰፋ እንደሚችል ስጋታቸውን አክለው የገለጹት ነዋሪዎች ኢህአዴግ ሰላማዊ መፍትሄ ሊፈልግ እንደሚገባ ከወዲሁ ጠይቀዋል። በጋምቤላ ክልል በሳንቲም የሚቸበቸበውና የተፈጥሮ ደን እያወደመ ያለው ኢንቨስትመንት የተወሳሰበ ችግር ማስከተሉ አይዘነጋም። በዚሁ ሳቢያ በርካታ ንጹሃን ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው። ክልሉን ከላይ ሆነው የሚመሩት አቶ አዲሱ ለገሰ መሆናቸው ይታወቃል።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ጉዳዩን አስመልክቶ ከኦስሎ ለጎልጉል አስተያየት ሲሰጡ “ባሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ላለፈ ወገኖች የሰላም ረፍት ይሁን፣ ፍትህ በልጅ ልጆቻችሁ ትፈርድላችኋለች፣ ፍትህ ሩቅ አይሆንም” በማለት ነበር የጀመሩት። አያይዘውም “ምንም እንኳ ባል ፖለቲከኛ ቢሆን ሚስትና ልጆች ምን አደረጉ? ህጻናትና ሴቶች በማያውቁት ጉዳይ ለምን ሰላባ ይሆናሉ? ቀደም ሲል አብረው የሚኖሩ ሰዎች ዛሬ ለምን ይጋጫሉ?” ሲሉ ችግሩ ሁሉ የሚመነጨው ኢህአዴግ ከሚከተለው ጎሳን መሰረት ያደረገ የከፋፍለህ ግዛው መርህ አንደሆነ ገልጸዋል።
“መመሪያ ሰጪው፣ ገዳዩ፣ አስገዳዩ፣ ቆሞ ተመልካቹ፣ … ሁሉም ከፍትህ አደባባይ አያመልጡም” ያሉት አቶ ኦባንግ “ዘርን እየለየ የሚከናወን ግድያ “ጄኖሳይድ” ነው። አኙዋኮች ላይ በጅምላ ከተከናወነው ጭፍጨፋ ለይተን አናየውም” ሲሉ በጉዳዩ ክፉኛ ማዘናቸውን አመልክተዋል።
የሚመሩት ድርጅት ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለና አስፈላጊ ነው የሚለውን ስራ እያከናወነ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ ሁሉም ያካባቢው ነዋሪዎች ሰፋሪም ሆነ የቀዬው ተወላጆች እንደቀድሞ በፍቅር ሊኖሩ የሚያስችላቸውን እሴቶች እንዲጠብቁ መክረዋል። በተለያዩ ያገሪቱ ክፍሎች ጎሳን እየለየ የሚካሄደው ግድያና ማፈናቀል እየሰፋ እንጂ እየቀነሰ ባለመሆኑ ስጋቱ ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል። በዚህ ከቀጠለና ህወሃት የቀበራቸው የጎሳ ፈንጂዎች ሲነዱ እሳቱ ሁሉንም ስለማይምር ሁሉም ዜጎች ጥንቃቄ እንዲወስዱ አሳስበዋል። ኢህአዴግም ችግሮችን ከማስፋት ይልቅ የሚቃለሉበትን አግባብ ለራሱ ሲል ሊከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል። ጎልጉል የዞኑንና የወረዳውን አስተዳደር ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ይሁን እንጂ የክልሉ ፖሊስ ዝርዝር መግለጫ ባይሰጥም የተባለው ቀውስ ስለመፈጠሩ አልካደም።
ምንጭ ጎልጉል 

No comments: