Wednesday, August 28, 2013

መንግሥት ለተፈጠረው ችግር በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ እንጠይቃለን! ሰማያዊ ፓርቲ

August 28, 2013
ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ


semayawi party's protest call in Addis Ababaፓርቲያችን ሰማያዊ በህገ መንግሥቱ በተደነገገው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱን ተጠቅሞ ለመንግሥት ጥያቄዎችን በማቅረብ ግንቦት 25/2ዐዐ5 ዓ/ም. ታላቅ ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ አድርጓል፡፡

መንግሥት ላቀረብናቸው ጥያቄዎች በሦስት ወር ውስጥ መልስ የማይሠጥ ከሆነ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ ጥያቄያችንን በድጋሚ በህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ እንደምናቀርብ በግንቦት 25/2ዐዐ5 ዓ/ም. በተደረገው ሠልፍ ላይ ለህዝብ ቃል በገባነው መሠረት ነሃሴ 26/2ዐዐ5 ዓ/ም. በድጋሚ ሰልፍ ጠርተን አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረግን መሆኑን ለህዝብ በልዩ ልዩ መገናኛ ዘዴዎች ገልፀናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለሰልፉ በሰላም መጠናቀቅ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግልን አዋጁ በሚጠይቀው መሠረት ለአዲስ አበባ መስተዳድር ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሰወቂያ ክፍል ጉዳዩን እንዲያውቀው አድርገናል፡፡

ይሁን እንጂ ፓርቲያችን ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ በጠራበት ግዜና ቦታ ላይ በሌላ አካል ሰልፉ መጠራቱን በትናንትናው ዕለት ነሀሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም በመንግሥት ቴሌቪዥን ዜና ሰምተናል፡፡ በተጨማሪም ለመንግሥት መዋቅር ዜጐች በዚህ ሰልፍ እንዲወጡ በግድ እንዲፈርሙ እየተደረገ መሆኑን ከአዲስ አበባ ኑዋሪዎች አረጋግጠናል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ አስፈላጊውን የህግ ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ነሐሴ 26/2ዐዐ5 ዓ/ም. በመስቀል አደባባይ የጠራውን ተቃውሞ ሰልፍ ለህዝብ ያሳወቀና አስፈላጊውን ዝግጅት ያጠናቀቀ በመሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ በጠራበት ቀንና ሠዓት በሌሎች አካላት የተጠራው ሰልፍ ከመረጃ እጥረት ከሆነ እንዲሠረዝ እየጠየቅን ይህ ካልሆነ ግን ሰማያዊ ፓርቲ በህጋዊ መብቱ የሚያደርገውን የተቃውሞ ሰልፍ ሆን ብሎ ለመረበሽና አቅጣጫውን ለማስቀየስና በዜጐች መካከል ግጭት ለመፍጠር የታቀደ ስለሆነ ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ መንግሥት መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብና የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት በአፅንዖት እንገልፃለን፡፡
በመጨረሻም መንግስት ዜጐችን ያለፈቃዳቸው በማስፈረም ተገደው ሰልፍ እንዲወጡ ማድረግ ህገ ወጥ ስለሆነ፣ በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን፡

No comments: