Friday, August 16, 2013

የኢህአዴግ አባላት ክርስቶፎር ስሚዝ በሚያረቁት ህግ ላይ የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ጀመሩ

ነሃሴ ፲(አስር)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከደጋፊዎቹ የመረጃ ለውውጥ ለመረዳት እንደተቻለው ኮንግረስ ማን ክሪስ ስሚዝ በቅርቡ በኢትዮጵያ ዙሪያ የግንቦት 7 መሪ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋን፣ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሀላፊ ሚ/ር ያማማቶ እና ሌሎችንም ታዋቂ ሰዎች በመጋበዝ በኢትዮጵያ ዙሪያ የተለያዩ ሀሳቦችን ማሰባሰባቸው ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችን እንድታከብርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን እንድትገነባ፣ ኮንግረሱ የህግ ረቂቅ እንደሚያዘጋጅ ሚ/ር ስሚዝ ገልጸዋል።

የህጉን መረቀቅ የተቃወሙት የኢህአዴግ ደጋፊዎች  ለሚ/ር ስሚዝ ደብዳቤ መላክ ጀምረዋል። በደብዳቤው ላይ ሚ/ር ስሚዝ በኢትዮጵያ መንግስት አሻባሪ የተባሉትን ሰዎች ለውውይት መጋበዛቸውን አውግዘዋል። በኢትዮጵያ ላይ የሚረቀቀው ህግ የአሜሪካንና የኢትዮጵያን ግንኙነት የሚያበላሽ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ በውጭ ተጽኖ አቋሟን የማትቀይር መሆኗንና ሚ/ር ስሚዝም ኢትዮጵያን ለመደገፍ የሚያስችል የህግ ረቂቅ እንዲያዘጋጁ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች እየፈረሙ በሚልኩት ደብዳቤ ላይ ተመልክቷል።

አስቸኳይ በሚል ርእስ ለኢህአዴግ አባላት በተላከው የኢሜል መልዕክት ላይ ህጉ የሚረቀቅ ከሆነ በኢትዮጵያ ላይ ከባድ ተጽኖ እንደሚያስከትል ተመልክቷል።

ህዳሴ ካውንስል የሚባለው የኢህአዴግ አባላትንና ደጋፊዎችን የያዘው ቡድን የድጋፍ ፊርማ የማሰባሰብ ተልእኮ የተሰጠው ሲሆን፣ በአጠቃላይ እስከ 10 ሺ የሚደረሱ ፊርማዎችን አሰባስቦ የመላክ እቅድ ተይዟል።
የ1997 ዓም ምርጫን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ በተመሳሳይ መንገድ የተረቀቀው ህግ ዲኤል ኤ ፓይፐር በተባለው ተቋም ድለላ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወቃል።

No comments: