Thursday, August 1, 2013

የወያኔ “የድህነት ቅነሳ ፓሊሲ” ለድሀው – “ላም አለኝ በሰማይ …”

ከወያኔ አሰልቺ ዲስኩሮች አንዱ “ልማት” በተለይም “ድህነት ቅነሳ” ነው። ወያኔ ስለ ፈጣን ልማትና ስለ ድህነት ቅነሳ ሲነገረን እነሆ ሁለት አስርታት አለፉ!!!
እርግጥ ነው ወያኔ የራሱን አባላት ድህነት ቀንሷል። የሌላው ኢትዮጵያዊ ድሀ ድህነት ግን እየጨመረ ነው። ያም ሆኖ ግን ወያኔ የራሱ ሹማምንት ከሕዝብ በዘረፉት ገንዘብ የገነቧቸውን ፎቆች እያሳየን “እነሆ ልማታችሁ” እያለ ይሳለቅብናል። በውሸቱ የተሞሉ የምርት መጠንና ምርታማነት መስፈርቶችን እያስነበበን እየራበን “ጠገብን”፤ እየታርዝን “ለበስን” እንድንል ያደርገናል። “ኮንዶሚኒየም አድላለሁ” እያለ እያጓጓን ያችኑ ትንሿ ጥሪታችንን ይነጥቀናል።
ወያኔ በልማት ስም ምን ያላደረገን ነገር አለ? ትምህርት ሳይኖር ዲግሪ እያሸከመ ቀልዶብን ዲግሪ ይዘን ለኮብልስቶን ማንጠፍ ሥራ ተወዳድረናል። ህክምና ሳይኖር በክሊኒኮች መብዛት ተደስታችሁ ጨፍሩ ብሎናል። በጨለማ ውስጥ ተቀምጠን ስለግድቦች መብዛትና ስለ መብራት ኃይል ምርት መትረፍረፍ መስክሩ ይለናል።
ስንቶቻችን ነን የዕለት ተዕለት ኑሮዓችን እና የወያኔ የልማት ዲስኩሮች አልጣጣም እያሉን የተቸገርነው? ፈረንጆችም እነዚያኑ የወያኔ ቁጥሮችን መልሰው ሲነግሩን ስንቶቻችን ነው ከቁጥሮች ጋር የተጣላነው? የወያኔ ልማት፤ የወያኔ ድህነት ቅነሳ ፓሊሲ “ላም አለኝ በሰማይ፤ ወተትዋን እማላይ” የሆነብን ስንቶቻችን ነን?
ወያኔ ሰጠኋቸው በሚለው ሳይሆን እኛ በበላነውና በለበስነው፣ ባገኘው የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች ኑሮዓችን ቢለካ ደረጃችን የት ይሆናል? በሚነገረን ሳይሆን በምንኖረው መጠን ትዳራችን ቢለካ ደረጃችን የት ነው?
ከድህነት መለኪያዎች ሁሉ የተሻለና የተሟላ ነው የሚባለው በእንግሊዝኛ Multidimensional Poverty Index የሚባለው ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ ነው። ይህን መለኪያ ሰዎች በእርግጥ ባገኙትና በተጠቀሙት ምርትና አገልግሎት መጠን ይነሳል። ሌሎች የድህነት መለኪያዎች መንግሥት አመረትኩ ወይም ሰጠሁ በሚለው ቁጥር ነው የሚነሱት። ውሸት በማይበዛባቸው አገራት በዚህም ተለካ በዚያ እጅግም ለውጥ የለውም። እኛጋ ግን ልዩነቱ የትየለሌ ነው።
ወያኔ የሚወዳቸው መለኪያዎች መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ልንገባ መቃረባችንን ይነግሩናል። እነሱ መሠረት ያደረጉት ወያኔ አመረትኩ፣ ሰጠሁ የሚለውን ነው። ኑሮዓችን እኛ የተቀበልነው መሠረት በሚያደርገው ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ ሲለካ ግን ውጤቱ ፈጽሞ ሌላ ነው።
የ2013 የአውሮፓውያን ዓመት የዓለም ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ ስታትስቲክስ ባለፈው ሣምንት ይፋ ተደርጓል። ዘገባው እንደሚያሳየው የዓለማችን የመጨረሻዎቹ አስር ድሀ አገሮች በሙሉ አፍሪቃ ውስጥ ነው ያሉት። ከእነዚህ የመጨረሻ አስር ድሀ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ አገራችን ናት።
አሳዛኙ ዜና ይህ ብቻ አይደለም።
ከአስሩ የመጨረሻ ድሀ አገሮች የመጨረሻዋ ኒጀር ስትሆን ከዚያ ቀጥላ የምትመጣው ኢትዮጵያ ነች። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛ የመጨረሻ ድሀ አገር ናት። በድህነት ለኢትዮጵያ የባሰች አገር ኒጀር ብቻ ነች። ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ብቻ ሳይሆን ሶማሊያ እንኳ ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው።
ይህ ምንን ይነግረናል?
በወያኔ ቴሌቪዥን የሚቀርብልን ማዕድ ምግብ አይሆነንም። ጆሮዓችን እስኪደነቁር “ልማት፤ ልማት” እየተባለ ስለተጮኸብን ማጀታችን አይሞላም። መራብና መታረዛችን ሳያንስ “ጠግባችኋል” እየተባለ የሚቀለድን መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል። እኛ እየተራብንና እየታረዝን ባዕዳን ቱጃሮች በመሬታችን ላይ በሀብት ላይ ሀብት የሚጨምሩ መሆኑ ያስከፋናል። እኛ በጨለማ ተውጠን የመብራት ኃይል የሚሸጥ መሆኑ ይቆጨናል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ሳንበላ በጥጋብ እንድናገሳ፤ ደሳሳ ጎጆዓችን እየፈረሰ “ልማት መጣ” እያልን እንድንጨፍር፤ በጨለማ እየኖርን ለግድብ መዋጮ የምንገፈግፍ ምስኪኖች ሆነናል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ በድህነታችን ላይ መጫወቱ መቆም አለበት ይላል። ግንቦት 7: “መሮናል፤ ከፍቶናል። ወያኔን ከነውሸቱ ልናወስግድ ተነስተናል። ለወያኔ የውሸት “ድህነት ቅነሳ” ጆሮዓችንን አንስጥ። ይልቁንም ወያኔን አስወግደን የመልማት እድላችንን በእጃችን እናስገባ፤ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ሲኖር ደግሞ የውሸት ሳይሆን የእውነት እንደምንለማ ባለሙሉ ተስፋዎች ነን” ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!



    No comments: