Saturday, August 17, 2013

የአንባገነኖች የስልጣን አለቅም ግብ-ግብ መጨረሻ ፤ ዉርደት ፣ እስር እና ሞት

ከበትረ ያዕቆብ
ባደጉትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት በቻሉት የምዕራቡ ሀገሮች አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ግለሰብ ሰላማዊ በሆነ የህዝብ ምርጫ ስልጣን ላይ ይወጣል፡፡ ግዳጁን ባጠናቀቀ ግዜ ወይም በወከለዉ ህዝብ ዘንድ አመኔታን ሲያጣ ደግሞ እንደ አወጣጡ ሁሉ በሰላም ከስልጣኑ ዉልቅ ይላል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ከዚህም በተለየ ሁኔታ መሪዎች በሀገር ላይ ከሚጋረጡ ፈተናዎች ጋር በተያያዘ ሀላፊነታችንን መወጣት አልቻልንም ሲሉ ተፈፀሙ ለሚሏቸዉ ስህተቶች ሁሉ ሀላፊነቱን በመዉሰድ ሌላ አቅምና እዉቀት ለሚፈቅድላቸዉ ሰዎች ስልጣናቸዉን አስረክበዉ በሰላምና በፍቅር ከነሙሉ ክብራቸዉ ሹልክ ይላሉ፡፡
አሁን አሁን ይህን መሰል ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር በብዙ ሀገሮች እየተስፋፋና እየተለመደ የመጣ ሲሆን ፤ ኃላ ቀር በሚባለዉ የአፍሪካ አህጉር ዉስጥ በሚገኙ አንዳንድ ሀገራት ጭምር መታየት ጀምሯል፡፡ ለምሳሌ ያህል ጋናን እና ጎረቤታችን የሆነችዉን ኬንያን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ዛሬም ቢሆን በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች መሰል ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ፈታኝ ሆኖ እንደቀጠለ ነዉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኋላ ቀር ሀገራት አሁንም ገዥዎች ወደ ስልጣን የሚወጡትም ሆነ ከስልጣናቸዉ የሚወርዱት ያዉ በጠመንጃ ወይም በህዝብ አመፅ ብቻ ነዉ፡፡ እዚህ ላይ ባለፉት 50 ዓመታት ዉስጥ በሀገራችን የተካሄዱ የስልጣን ሽግግሮች አይነተኛ ማሳያ ይሆናሉ፡፡
ብዙዉን ግዜ በእንደዚህ ዓይነት በሐይል በታጀበ የስልጣን ሽግግር ወቅት ስልጣናቸዉን የሙጥኝ የሚሉ አንባገነኖች መጨረሻቸዉ ዘግናኝና አሳፋሪ ዉድቀት ነዉ፡፡ ብዙዎቹ በስልጣን ልቀቅ አለቅም ትግሉ ሕይወታቸዉን ሲያጡ የቀሩት ደግሞ ስልጣናቸዉን ሲነጠቁ በስልጣን ዘመናቸዉ በፈፀሙት ግፍ ስም ወደ ግዞት ይወረወራሉ ወይም ከተወለዱባት እናት ሀገራቸዉ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ ተዋርደዉ ይሰደዳሉ ፤ አንዳንዴም ከዚህ የከፋ ነገር ይገጥማቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከቱንዚያ ተነስቶ የአረቡን ዓለም ያዳረሰዉ አሁንም የት ላይ እንደሚቋጭ ያልታወቀዉ የፀደዩ አቢዎትን ተከትሎ ከስልጣናቸዉ በሰላም እንዲወርዱ ሲለመኑ አሻፈረኝ በማለት ከህዝብ ጋር ግብ ግብ የገጠሙትን የኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊን መጨረሻ መመልከት ይቻላል፡፡ ጋዳፊ ስልጣን በሰላም አስረክቦ ከነሙሉ ክብሩ ሹልክ ማለት እየቻለ በእብሪት ተወጥሮ አሻፈረኝ በማለቱ ከራሱ አሳፋሪና ወራዳ ሞት ባሻገር የልጆቹን ህይወት እንደ ቅጠል አርግፏል፡፡
በተመሳሳይ ስልጣን በሰላም እንዲያስረክብ ሲጠየቅ እንቢ ሲል የኖረዉ የግብፁ ሙባረክም አረፍ ብሎ ሰላማዊ አየር እየተነፈሰ ጣፋጭ ህይወት ከቤተሰቦቹ ጋር በሚያጣጥምበት የእርጅና ዘመኑ ተዋርዶ ወደ እስር ቤት የተወረወረ ሲሆን ፤ የእርሱ ጦስ ለልጁም ሊተርፍ ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እነሎረንስ ባግቦን ፣ ቤን አሊንንና ሌላ በርካታ አንባገነኖችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
እንግዲህ የሀገራችንንም ታሪክ ስንመለከት በአፄ ሐይለ ስላሴና ባለስልጣናቶቻቸዉ የደረሰዉ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ንጉሱን ጨምሮ ብዙ ባለስልጣኖቻቸዉ በያሉበት እየተለቀሙ የሞት እራት ነበር የሆኑት፡፡ እንደዚያ መለኮታዊ ሐይል ያላቸዉ ይመስል ስንት ሲባሉ የነበሩት ንጉስ በክብር የመቀበር ወግ እንኳን አልደረሳቸም፡፡ በተመሳሳዩ እነርሱን ተክትለዉ ወደ ስልጣን በመጡት የደርግ ባለስልጣናት ላይም የደረሰዉ ያዉ የተለመደዉ ዉርደት ፣ እስር እና ሞት ነበር፡፡ ብዙወች በየጦር ግንባሩ የጥይት ሲሳይ ሲሆኑ ፤ የተቀሩትም ዛሬ በየ እስር ቤቱ ተወርዉረዉ በሚያሳዝን ሁኔታ ዉስጥ ይገኛሉ፡፡ ያገዛዙ ቁኝጮ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ሐይለማርያምም ቢሆኑ መኮብለል ቢሳካላቸዉም እንኳን የዉርደት ማቅ ከመከናነብ ግን አላመለጡም፡፡ በተሰደዱበት አገርም ቢሆን የተዝናና ህይወት ሳይሆን የገጠማቸዉ ተቃራኒዉ ነዉ፡-ፍርሀትና ሰቀቀን የበዛበት ህይወት፡፡
የኢህአዴግ ባለስልጣናት የቁልቁለት መንገድ
ምንም እንኳን የአንባገነኖች ከስልጣን አንለቅም ግብ ግብ ዉጤቱ ከላይ እንዳየነዉ በጣም የከፋ ቢሆንም የወቅቱ የሀገራችን መሪዎችና ባለስልጣናቱ ከታሪክ መማር አቅቷቸዉ የህዝብ የሆነን ስልጣን እደግመዋለሁ የህዝብ የሆነን ስልጣን ሙጭጭ በማለት ወደ ዉድቀት አፋፍ በፍጥነት እየተንደረደሩ ይገኛል፡፡
እንደሚታወቀዉ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከስልጣን ዉረዱ አንወርድም ግብግቡን በ1997 ከተካሄደዉ ሀገር አቀፍ ምርጫ ማግስት ጀምሮ በይፋ የጀመሩት ሲሆን ፤ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተቀዋሚ ፓርቲዎችን አመራሮች እና አባላትን በማሳደድ እንዲሁም የነፃዉን ፕሬስ ዉጤቶች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በማጥፋትና ጋዜጠኞቻቸዉንም በሐሰት ዉንጀላ በግፍ በማሰር አፈናዉን ከምን ግዜዉም በላይ አጠናክረዉ ቀጥለዋል፡፡
ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ የኑሮ ፈተና ፣ የፍትህ ማጣት ፣ ጭቆና እና እንግልት… የበዛበት ምስኪን ኢትዮጵያዊ ብሶቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጦ ዛሬ ለመፈንዳት ቋፍ ላይ ይገኛል፡፡ እንግዲህ ይህ በግልፅ የሚያመለክተዉ በስልጣን ላይ የሚገኙ ባለስልጣናት በታሪካችን እንዳየናቸዉ እና በነኮሎኔል ጋዳፊ እንደደረሰዉ ሁሉ የከፋ አወዳደቅ ለመዉደቅ ቀናቸዉን እየቆጠሩ እንደሆነ ነዉ፡፡
በተለይም የህወሓት ጠንሳሽና የኢህአዴግ መስራቹ እንዲሁም ሀገሪቱን ለ21 አመታት በመዳፋ አስገብቶ የገዛዉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህመም ከስልጣኑ ከተገለለበት ቆይቶም ከሞተበት ግዜ ጀምሮ በብሶት ተወጥሮ የኖረዉ ጭቁን ህዝብ ከምግዜዉም በላይ ለለዉጥ የበለጠ በማቆብቆብ ላይ ነዉ፡፡ እዚህ ላይ በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ እንዲሁም በጎንደር እና ደሴ ከተሞች የተካሄዱት ህዝባዊ ተቃዉሞዎች የሚያስብ ህሊና ላለዉ ሰዉ ብዙ ያስተላለፉት መልዕክት አለ፡፡
በተያያዘም አገዛዙ ለርካሽ ትርፍ ሲል የፈለሰፈዉ የጎሳ ፖለቲካ ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትር መለሽ ዜናዊን ሞት ተከትሎ በተነሳዉ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት በራሱ በኢህአዴግ ላይ የማይጠግኑት ትልቅ ስንጥቅ እየፈጠረ ሲሆን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ስልጣናቸዉ መከታ በሚቆጥሩት ጦር ዉስጥም ትልቅ መከፋፈል እያመጣ ስለመሆኑ መረጃዎች እየጠቆሙ ይገኛል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ አለማቀፋዊ ጫናዉ በዛዉ ልክ እየበረታ ሄዷል፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ ከህዝቡ ቁጣ ጋር ተደማምሮ አገዛዙን ከምን ግዜዉም በላይ ከዉድቀት አፋፍ ላይ አድርሶታል ማለት ይቻላል፡፡
ሆኖም ግን በጣም የሚያሳዝነዉ ፤ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም “ለአንዳንድ ሰዎች ቁልቁለት ቁልቁለት መሆኑ የሚታወቃቸዉ ወርደዉ ወርደዉ ወድቀዉ ሲከሰከሱ ነዉ” ሲሉ “አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ” በሚለዉ መፅሐፋቸዉ እንደገለፁት ሁሉ አገዛዙ እንዲህ ከዉድቀት አፋፍ ላይ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ባለስልጣናቱ ከአጠገባቸዉ በሞት የተለዩትን የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ስም እንደ ዳዊት ቃል እየደጋገሙ እና የማይጨበጥ ተስፋ እየሰበኩ ጭቆናቸዉን ለማስቀጠል ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡
በሰከነ አዕምሮ በማሰብ የህዝቡን የዲሞክራሲና የፍትህ ጥያቄ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመመለስና ሌላም የህዝቡን ቁጣ ማብረጃ እርምጃዎችን በመዉሰድ ከፊታቸዉ እየመጣ ካለዉ አስፈሪ ሕዝባዊ ማዕበል እንደማምለጥ ፤ እራሳቸዉንና ቤተሰቦቻቸዉን ከሚመጣዉ መዓት እንደማዳን እነሱ ግን በጭፍን አዕምሮአቸዉ ስልጣናቸዉን ሙጭጭ እንዳሉ የማያዋጣ ግብ ግብ ከህዝብ ጋር ይዘዋል፡፡ የዚህ ግብ ግብ መጨረሻም እየየቀረበ ይገኛል፡፡
ምንም እንኳን ያለፉትን 21 አመታት አንዴ በጉልበት አንዴ በማምታታት ማለፍ ቢቻልም ከዚህ በኋላ ግን ያን መድገም የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በፍትህ ፣ ዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር እጦት እንዲሁም በድህነት እና ለቁጥር በሚታክቱ ማህበራዊ ችግሮች የሚያቃትትን ህዝብ አይዞህ ኮንዶሚንየም ልገነባልህ ነዉ ፣ ባቡር እየመጣልህ ነዉ ፣ 11 ፐርሰንት እድገት… ቅብርጥሴ ማለት ብዙ እርቀት አያስጉዝም ፤ ከሚመጣዉ መዓበልም አያድንም ባይ ነኝ ፡፡
መፍትሄ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅር ባይ ነዉ፡፡ እንኳን ለአብራኮቹ ክፋይ ነዉና ለዉጭ ጠላት እንኳን ቢሆን ይንን ይቅር ባይነቱን አይነፍግም፡፡ ስለዚህ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ይህችንን የወገናቸዉን ደግነት በመረዳት ጊዜ ሳይሰጡ ለፈፀሙት በደል ይቅርታ መጠየቅ እና የህዝቡን የፍትህና የዲሞክራሲ ጥያቄ መመለስ ይኖርባቸዋል ብየ አምናለሁ፡፡ ይህንን ማድረግ ሽንፈት ሳይሆን ድል ነዉ ፤ ሞኝነት ሳይሆን ብልጠት ወይም የፖለቲካ ብስለት ነዉ፡፡
እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ይህንን በመፈፀማቸዉ እራሳቸዉንና ቤተሰቦቻቸዉን ከሚመጣባቸዉ ችግር ከማዉጣት ባሻገር ስማቸዉንም በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ በበጎ ይፅፋሉ፡፡ በህዝቡም ዘንድ ትልቅ ከበሬታን ይጎናፀፋሉ፡፡ በተያያዙት የጭፍን ጉዞ ከቀጠሉ ግን በቅርቡ እነርሱም በታሪክ እንዳየናቸዉ ግዞት ቤታቸዉ እንግልት ሕይወታቸዉ እንደሚሆን ጥርጥር የለዉም ፤ ሲልም ከዚያ የከፋ ነገር ሊገጥማቸዉም ይችላል፡፡

No comments: