Wednesday, August 28, 2013

በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ሰማያዊ ፓርቲ እና ኢህአዴግ በየፊናቸው ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተከትሎ አዝማሚያው ወደ ውጥረት እያመራ መሆኑን ታዛቢዎች ገለጹ።

ነሃሴ ፳፩(ሃያ አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰማያዊ ፓርቲ ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ ለነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓመተምህረት ሰልፍ እንደሚጠራ አስታውቆ የቅስቀሳ ሥራ መሥራት በጀመረበት ጊዜ፤ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ሰሞኑን  በዚያው ቀን ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ ማቅረቡ ያታወቃል።
በተለይ በኢህአዴግ የሰልፍ ጥሪ  የሴትና ወጣት ማህበራት፣የመንግስት ሠራተኞች፣ የሀይማኖት ተቋማትና  ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጭምር በግዳጅ እንዲወጡ መታዘዛቸው፤ ሁኔታውን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይወስደዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰማያዊ ፓርቲ፤የ አፍሪካ መሪዎች አዲስ አበባ ላይ በተሰበሰቡበት ወቅት ሰልፍ ለማድረግ  ወስኖ ሳለ፤  የአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ክፍል ፤ወቅቱ የመሪዎች ስብሰባ ከመሆኑ አንፃር በዕለቱ በቂ ሀይል እንደሌለውና ሰልፉን ለሳምንት እንዲያሸጋግሩ በጠየቀው መሰረት፤ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን ማሸጋገሩ ይታወሳል።
ይሁንና ያን ውሳኔ ያሳለፈው የመስተዳድሩ የሰልፍ ፈቃድ ክፍል ፤ ኢህአዴግ-ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ሊያደርግ ባቀደበት ተመሣሳይ ቀንና ከተማ ውስጥ ሰልፍ ለማድግ ሢነሳ ምንም አለማለቱ ታዛቢዎችን አስገርሟል።
ኢህአዴግ-የሸህ ኑሩን ሞት ተከትሎ በሌሎች ክልሎች እንዳደረገው ሁሉ በአዲስ አበባ ሊያደርገው በተዘጋጀው ሰልፍም የሙስሊሞችን የመብት ይከበር እንቅስቃሴ ከሽብርተኝነትና ከጽንፈኝነት ጋር በማያያዝ በሰልፈኛው ለማስወገዝ መዘጋጀቱ ታውቋል።
ከዚህም ሌላ የገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎች ሰልፍ በሚወጡበት ዕለት -ኢህአዴግ የከተማዋን ነዋሪዎች በግዳጅ “እኔን ደግፋችሁ ውጡ”ማለቱ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ አላስፈላጊ መቃቃርን፣ መወጋገዝንና መለያዬትን  ለመፍጠር በማሰብ  ጭምር ነው የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰነዘሩ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ  መንግስት  የጠራውን ሰልፍ እንዲሰረዝ ሰማያዊ ፓርቲ ጠየቀ።
ፓርቲው፦”መንግሥት ለተፈጠረው ችግር በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ እንጠይቃለን!!”በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤ ሰማያዊ  ፓርቲ ግንቦት 25/2ዐዐ5 ዓ/ም. ታላቅ ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ ማድረጉን አስታውሶ፦” መንግሥት ላቀረብናቸው ጥያቄዎች በሦስት ወር ውስጥ መልስ የማይሠጥ ከሆነ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ ጥያቄያችንን በድጋሚ በህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ እንደምናቀርብ በግንቦት 25/2ዐዐ5 ዓ/ም. በተደረገው ሠልፍ ላይ ለህዝብ ቃል በገባነው መሠረት ነሃሴ 26/2ዐዐ5 ዓ/ም. በድጋሚ ሰልፍ ጠርተን አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረግን መሆኑን ለህዝብ በልዩ ልዩ መገናኛ ዘዴዎች ገልፀናል” ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ለሰልፉ በሰላም መጠናቀቅ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግልን አዋጁ በሚጠይቀው መሠረት ለአዲስ አበባ መስተዳድር ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማስታወቂያ ክፍል ጉዳዩን እንዲያውቀው አድርገናል ብሏል-ሰማያዊ ፓርቲ።
ይሁን እንጂ ፓርቲያችን የተቃውሞ ሰልፍ በጠራበት ግዜና ቦታ ላይ በሌላ አካል ሰልፉ መጠራቱን በትናንትናው ዕለት ነሀሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም በመንግሥት ቴሌቪዥን ዜና ሰምተናል ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ከዚህም በላይ  የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም  ዜጐች በዚህ ሰልፍ ይገኙ ዘንድ  በግድ እንዲፈርሙ እየተደረገ መሆኑን ከአዲስ አበባ ኗሪዎች አረጋግጠናል ሲል አትቷል።
ሰማያዊ ፓርቲ አስፈላጊውን የህግ ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ነሐሴ 26/2ዐዐ5 ዓ/ም በመስቀል አደባባይ የጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ለህዝብ ያሳወቀና አስፈላጊውን ዝግጅት ያጠናቀቀ በመሆኑም፤ ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ በጠራበት ቀንና ሠዓት በሌሎች አካላት የተጠራው ሰልፍ ከመረጃ እጥረት ከሆነ እንዲሠረዝ እንጠይቃለን ሲልም  ኢህአዴግ የጠራውን ሰልፍ እንዲሰርዝ  ጠይቋ ል።
ሰማያዊ ፓርቲ በማያያዝም፦”ይህ ካልሆነ ግን ሰማያዊ ፓርቲ በህጋዊ መብቱ የሚያደርገውን የተቃውሞ ሰልፍ ሆን ብሎ ለመረበሽና አቅጣጫውን ለማስቀየስና በዜጐች መካከል ግጭት ለመፍጠር የታቀደ ስለሆነ ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ መንግሥት መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብና የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት በአፅንዖት እንገልፃለን፡፡” በማለት አሣስቧል።

No comments: