Thursday, August 1, 2013

ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት እንዲቆምላቸው ጥሪ ቀረበ

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአፍሪካ ኅብረት) መሥራች ለሆኑት ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ተጠየቀ፡፡

ይህንን የጠየቁት የድርጅቱ/የኅብረቱ 50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ ክብረ በዓልን ለማክበርና መሥራቾች አባቶችን ለመዘከር ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው ውይይት ላይ ከተገኙ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ነው፡፡

ከዛሬ ሃምሳ ዓመታት በፊት የድርጅቱ/ኅብረቱ መሥራች ስብሰባ በተካሄደበት አፍሪካ አዳራሽ ውስጥ በተከናወነው ውይይት ላይ የተገኙት እነዚሁ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፣  ሐውልቱ መቆም ያለበት በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ፣ አለበለዚያም በደርግ ሥርዓት የሌኒን ሐውልት ቆሞበት በነበረው ሥፍራ ነው፡፡

ለሐውልቱም ግንባታ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በአገር ውስጥና በውጭ  የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ የበጐ ሥራቸውን ፈለግ ተከትሎ በመንቀሳቀስ ላይ ለሚገኘው ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበርም የማቴሪያልና የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ወደ ኋላ  እንደማይሉ አስታውቀዋል፡፡

ማኅበሩ ባዘጋጀው በዚሁ ስብሰባ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ለአፍሪካ ነፃነት ትግልና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ባበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላይ ያተኮሩ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎች በዘመኑ የሥራው ተካፋይ በነበሩና ታሪኩን በተመራመሩ ፈቃደኛ ሰዎች አማካይነት ቀርቧል፡፡ ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡትም መካከል የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ፣ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፣ አቶ ተሾመ ገብረ ማርያም፣ አምባሳደር ብርሃነ ደሬሳ፣ ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰና አቶ አብደላ መሐመድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ፓናሊስቶቹ በየተራ ካቀረቡዋቸው ጽሑፎች ለመረዳት እንደተቻለው፣ ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገሮች ካዛብላንካና ሞኖሮቪያ በተባሉ ሁለት ቡድኖች በተከፋፈሉብት ወቅት አገሮቹን ለማቀራረብና ወደ አንድነት እንዲመጡ ለማድረግ፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ  ጥበብ የተላበሰ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷዋል፡፡

በቅኝ ግዛት ቀንበር ሲማቅቁ የነበሩ አገሮች ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ለማድረግ የሚያስችል ግንባር ቀደም የሆነ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ የነፃነት ታጋዮችን በማበረታታትና  በመደገፍና ለበርካታ አገሮች ወጣቶች ነፃ የትምህርት ዕድል  በመስጠት፣  ታሪክ የማይረሳውና ተወዳዳሪ የማይገኝለት አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተወስቷል፡፡

በተለይም ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ወጣቱ ከተማ ይፍሩ፣ የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ ቡድኖችን በማሳመንና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ምክንያት በሆነው የ1955 ዓ.ም የመሪዎች ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የተጫወቱት ሚና ዝንት ዓለም ሲወሳ እንደሚኖር አስረድተዋል፡፡

በጉባዔው ወቅት አፄ ኃይለ ሥላሴ ጉባዔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ሳይመሠረትና የድርጅቱን ቻርተር ሳያፀድቅ መጠናቀቅ እንደሌለበት አጥብቀው ማሳሰባቸውን፣ ይህም ማሳሰቢያቸው የኋላ ኋላ ፍሬያማ ውጤት ማስገኘቱን ምቤኪ አስረድተዋል፡፡


የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ናሁሰናይ አርዓያ፣ “ከማኅበሩ የትኩረት አቅጣጫዎች አንደኛው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን ፈተና እጅግ በጣም በላቀ ውጤት ያስመዘገቡና በቤተሰቦቻቸው ችግር ምክንያት የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለመቀጠል ለማይችሉ ወጣቶች የገንዘብ ድጐማ በመስጠት ማበረታታት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከዘጠኝ ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ 300 ተማሪዎች ወርኃዊ የገንዘብ ድጐማ አድርጓል፤” ብለዋል፡፡

ማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከተመራቂዎቹም መካከል 69 በሕክምና፣  26 ደግሞ በምህንድስና የተመረቁ ናቸው፡፡  ማኅበሩ እጅግ በጣም ጐበዝና እጅግ በጣም ችግረኛ ለሆኑ ወጣቶች የሚደጉመው ከግለሰቦችና ከአንዳንድ ድርጅቶች በዕርዳታ በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ ማኅበሩ በድጐማ የተወሰነው ሙሉ ድጋፍ የማድረግ አቅም ስለሌለው ነው፡፡ በዚህም ውጤት አልረካም፡፡  በገቢ  ምንጭ እጦት ምክንያት ቀጣይነቱ አጠራጣሪ ነው፤” በማለት  የቦርዱ ሊቀመንበር አስረድተዋል፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር በአዋጅ ቁጥር 253/51 የተቋቋመው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጐ አድራጐት ድርጅት ተቀጽላ ነው፡፡ ሆኖም የደርግ መንግሥት የቀድሞውን ድርጅቱን አስወግዶ ሀብቱን በሙሉ ስለወረሰው ሥራው ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ማኅበሩም በ1991 ዓ.ም የቀድሞውን ድርጅት መሰል ሥራ በከፊልም ቢሆን ለማከናወን የንጉሡ አድናቂዎችና አገር ወዳድ በሆኑ 24 ኢትዮጵያውያን መመሥረቱ ተገልጿል፡፡

No comments: